Numbers 6

የናዝራዊነት ሥርዐት

1 እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤ 2“እስራኤላውያንን ተናገራቸው፤ እንዲህም በላቸው፣ ‘ወንድም ሆነ ሴት ናዝራዊ ይሆን ዘንድ ራሱን ለእግዚአብሔር (ያህዌ) ለመለየት ስእለት ቢሳል፣ 3ከወይን ጠጅና ከሌላም ከሚያሰክር መጠጥ ይታቀብ፤ የወይንም ሆነ የሚያሰክር የሌላ መጠጥ ኾምጣጤ አይጠጣ፤ እንዲሁም የወይን ጭማቂ አይጠጣ፤ የወይን ፍሬም ሆነ ዘቢብ አይብላ። 4በናዝራዊነቱ ወቅት ከወይን ተክል የሚገኘውን ማንኛውም ነገር፣ የወይኑን ዘር፣ ግልፋፊውንም እንኳ ቢሆን አይብላ።

5“ ‘ስእለት ተስሎ ራሱን በለየበት ጊዜ ሁሉ ምላጭ ራሱን አይንካው፤ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የተለየበት ጊዜ እስኪያበቃ ድረስ የተቀደሰ ይሁን፤ የራስ ጠጕሩንም ያሳድግ። 6ራሱን ለእግዚአብሔር (ያህዌ) በለየበት ጊዜ ሁሉ ወደ ሬሳ አይቅረብ። 7ራሱን ለእግዚአብሔር (ኤሎሂም) የለየበት ምልክት በራሱ ላይ ስላለ አባቱም ይሁን እናቱ፣ ወንድሙም ይሁን እኅቱ ቢሞቱ ለእነርሱ ሲል እንኳ ራሱን አያርክስ። 8ራሱን በለየበት ጊዜ ሁሉ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የተቀደሰ ነው።

9“ ‘ድንገት ሰው አጠገቡ ሞቶ ለእግዚአብሔር የተለየበትን ጠጕሩን ቢያረክስበት፣ በሚነጻበት ዕለት ማለት በሰባተኛው ቀን ጠጕሩን ይላጭ። 10በስምንተኛው ቀን ሁለት ዋኖስ ወይም ሁለት የርግብ ጫጩቶች ይዞ ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ወደ ካህኑ ዘንድ ያምጣ። 11ካህኑም አንዱን ለኀጢአት መሥዋዕት ሌላውን ማስተስረያ እንዲሆንለት የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጎ ያቅርበው፤ በሬሳ አጠገብ በመገኘቱ ኀጢአት ሠርቷልና። በዚያኑ ዕለት ጠጕሩን ይቀድስ። 12ራሱን የተለየ ያደረገበትን ጊዜ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) መቀደስ አለበት፤ እንዲሁም የአንድ ዓመት ተባት ጠቦት የበደል መሥዋዕት አድርጎ ያምጣ። ያለፉት ቀኖች አይቈጠሩም፤ በተለየበት ጊዜ ረክሷልና።

13“ ‘እንግዲህ ናዝራዊ የመለየቱ ጊዜ ሲያበቃ ሥርዐቱ ይህ ነው፤ ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ እንዲመጣ ይደረጋል። 14እዚያም መሥዋዕቱን ለእግዚአብሔር (ያህዌ) ያቅርብ፤ ይኸውም፣ እንከን የሌለበት የአንድ ዓመት ተባዕት ጠቦት ለሚቃጠል መሥዋዕት፣ እንከን የሌለበት የአንድ ዓመት እንስት ጠቦት ለኀጢአት መሥዋዕት እንዲሁም እንከን የሌለበት አውራ በግ ለኅብረት መሥዋዕት
በተለምዶ የድነት መሥዋዕት ማለት ነው።
ሲሆን፣
15ከእነዚህም ጋር የሚቀርበውን የእህልና የመጠጥ ቍርባን ያለ እርሾ የተጋገረ ቂጣ ማለት ከላመ ዱቄት በዘይት የተለወሱ ዕንጐቻዎች እንዲሁም በስሱ የተጋገረና ዘይት የተቀባ ስስ ቂጣ ያምጣ።

16“ ‘ካህኑ እነዚህን የኀጢአት መሥዋዕትና የሚቃጠል መሥዋዕት በማድረግ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ያቀርባል። 17በመሶብ ያለውን እርሾ የሌለበት ቂጣ እንዲሁም አውራ በጉን የኅብረት መሥዋዕት አድርጎ ከእህሉና ከመጠጡ ቍርባን ጋር ለእግዚአብሔር (ያህዌ) ያቅርብ።

18“ ‘ከዚያም ናዝራዊው ተስሎ የተለየበትን ጠጕር በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ይላጨው፤ ጠጕሩንም ወስዶ ከኅብረቱ መሥዋዕት ሥር በሚነደው እሳት ውስጥ ይጨምረው።

19“ ‘ናዝራዊው ተስሎ የተለየበትን ጠጕር ከተላጨ በኋላ፣ ካህኑ የተቀቀለውን የአውራውን በግ ወርች እንዲሁም ከመሶቡ ላይ እርሾ የሌለበትን አንድ ወፍራምና አንድ ስስ ቂጣ ወስዶ ናዝራዊው ያስይዘው 20ከዚያም ካህኑ የሚወዘወዝ መሥዋዕት በማድረግ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ይወዘውዛቸዋል፤ እነዚህም የተቀደሱ ናቸው። ከተወዘወዘው ፍርምባና ከቀረበው ወርች ጋር የተቀደሱ የካህኑ ድርሻ ይሆናሉ። ከዚህ በኋላ ናዝራዊው የወይን ጠጅ መጠጣት ይችላል።

21“ ‘ስእለቱን ለመፈጸም ለእግዚአብሔር (ያህዌ) ለሚሳል ናዝራዊ ሕጉ ይኸው ነው፤ ሊቀርብ ከሚችለው በላይ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) ለመስጠት ቃል ለሚገባው ነገር እንደ ናዝራዊነቱ በተሳለው መሠረት መሆን አለበት። በናዝራዊነት ሕግ መሠረት የተሳለውን ስእለት መፈጸም ይገባዋል።’ ”

የካህናት ቃለ ቡራኬ

22 እግዚአብሔርም (ያህዌ) ሙሴን አለው፤ 23“አሮንንና ልጆቹን እንዲህ በላቸው፤ ‘እስራኤላውያንን በምትባርኩበት ጊዜ እንዲህ በሏቸው፤

24“ ‘እግዚአብሔር (ያህዌ) ይባርክህ፤
ይጠብቅህም፤
25 እግዚአብሔር (ያህዌ) ፊቱን ያብራልህ፤
ይራራልህም፤
26 እግዚአብሔር (ያህዌ) ፊቱን ይመልስልህ፤
ሰላሙንም ይስጥህ።’
27“በዚህ ሁኔታ ስሜን በእስራኤላውያን ላይ ያደርጋሉ፤ እኔም እባርካቸዋለሁ።”

Copyright information for AmhNASV